የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አነስተኛና ቀላል የጦር መሣሪያዎችን አስወገደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እንዲወገዱ በጥናት የለያቸውን የተለያዩ አነስተኛና ቀላል የጦር መሳሪያዎችን አስወግዷል።
የማስወገድ ሂደቱን የክልልና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በተገኙበት ማከናወኑም ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ተሻለ ሚቆሬ ÷ ዛሬ የተከናወነው ተግባር የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ለመተግበር ከሚከናወኑ በርካታ ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥርን ተግባራዊ ለማድረግ ዓለም አቀፍ የህግ ማዕቀፎችን የተቀበለችና ሕጋዊ አሰራሮችን የዘረጋች መሆኗንም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም “ጥቅም ላይ የማይውሉ የጦር መሣሪያዎች በሰው ልጅ ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት አስቀድመን በዚህ መልክ ማስወገድ አለብን ” ማለታቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የጋፋት አርማመንት ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሌተናል ኮሎኔል ግዛቸው ተስፋዬ በበኩላቸው÷ በሚወገዱ መሣሪያዎች ላይ ያሉ ብረቶች በቀላሉ በገበያ ላይ የማይገኙ ውድ ብረቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ብረቶቹ በጋፋት አርማመንት ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ሂደት ውስጥ አልፈው እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ በውጭ ምንዛሬ ተገዝተው የሚመጡ መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደሚቻል ተናግረዋል።