ዩክሬን ሩሲያ የተኮሰቻቸውን 5 ሚሳኤሎችንና 48 ድሮኖችን መጣሏን ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዩክሬን አየር ሃይል ሩሲያ ሌሊቱን ያስወነጨፈቻቸውን አምስት ሚሳኤሎች እና ከ53 ድሮኖች ውስጥ 48ቱን መትቶ መጣሉን የዩክሬን ጦር አስታውቋል፡፡
የሩስያ ጦር በኪየቭ አካባቢ በድሮኖች እና ሚሳኤሎች ጥቃት በመፈፀም ከኢንዱስትሪ ተቋማቶች በአንዱ ላይ የቃጠሎ አደጋ መድረሱን የአካባቢው አስተዳደር ገልጿል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም ማለዳ ላይ እሳቱን የማጥፋት ሥራ ማከናወናቸው የተገለጸ ሲሆን÷ በጥቃቱ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩ ተመላክቷል።
የየአካባቢዎቹ ግዛት አስተዳደሮችም ጥቃት መሰንዘሩን በማመልከት ነገር ግን በግዛቶቻቸው ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱን ተናግረዋል፡፡
የዩክሬን ጦር በበኩሉ ከኪቭ በተጨማሪ በደቡባዊ ኦዴሳ ግዛት ሰባት፣ በኬርሰን ግዛት ሶስት እንዲሁም በማይኮላይቭ ግዛት ሁለት ድሮኖች መውደቃቸውን ገልጿል።
ጥቃቱ ምንም አይነት የኃይል መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት እንዳላደረሰ የዩክሬን ምክትል የኢነርጂ ሚኒስትር ማይኮላ ኮሊስኒክ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
ሩሲያ በዚህ የፀደይ ወቅት የዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማትን ዒላማ በማድረግ በመላ ሀገሪቱ የኃይል መቆራረጥን ማስከተሏን ሬውተርስ ዘግቧል።