ኢንስቲትዩቱ የቲቢ ህክምናን ከ24 ወራት ወደ 9 ወራት ዝቅ የሚያደርግ የምርምር ውጤት ማግኘቱን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት 24 ወራት ይወስድ የነበረውን መድሃኒት የተላመደ የቲቢ ህክምናን ወደ ዘጠኝ ወራት ዝቅ የሚያደርግ የምርምር ውጤት ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ 54ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀው የጉባኤና ጉብኝት መርሃ ግብር የጤናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት፣ የልማት አጋሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።
መርሃ ግብሩ ኢንስቲትዩቱ በምርምር ያለው አበርክቶና በሚያከናውናቸው ስራዎች ዙሪያ ገለጻ በማድረግ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ነው ተመላክቷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር)፤ ኢንስቲትዩቱ በወባ፣ ስጋ ደዌ፣ ቲቢ፣ ማጅራት ገትር፣ ኮሌራ፣ የአንጀት ተስቦ እንዲሁም በባክቴሪያ የሚመጡ በሽታዎች ላይ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለ24 ወራት ይሰጥ የነበረውን መድሃኒት የተላመደ የቲቢ ህክምናን ወደ ዘጠኝ ወራት ዝቅ የሚያደርግ የምርምር ውጤት ማግኘቱንም ጠቁመዋል፡፡
የምርምር ውጤቱ በዓለም ጤና ድርጅት እውቅና ተሰጥቶት ስራ ላይ የዋለ ሲሆን ላንሴት በተባለ ዓለም አቀፍ ጆርናል ላይ መውጣቱንም ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የጤና ባዮ ቴክኖሎጂን ጨምሮ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በምርምር ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሰራ መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።