የዴሞክራሲ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነው ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል – አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዴሞክራሲ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነው ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ አስታወቁ።
‘የዴሞክራሲ ተቋማት ሚና በሀገረ መንግሥት ግንባታ’ በሚል ርዕስ በምክር ቤቱ እና በጀርመኑ ኮንራድ አዴኑር እስቲፍተንግ ቲንክ ታንክ ፖሊሲ ኢንስቲቲዩት በጋራ የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለፌዴራልና ለክልል ምክር ቤት አመራሮችና ለዴሞክራሲ ተቋማት ኃላፊዎች በቢሸፍቱ ከተማ እየተሰጠ ነው።
በስልጠናው ላይ አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ ምክር ቤቶች የሕዝብ ተሳትፎን በማረጋገጥ፣ ውጤታማ የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት፣ በክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎች የህዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የዴሞክራሲ ተቋማት ለሀገረ መንግስት ግንባታ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ተቋማቱ ነፃና ገለልተኛ በመሆን ሃላፊነታቸውን መፈፀም እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
በተለይ የሚዲያ ተቋማት ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ፣ ህብረተሰቡ ውስጥ የሚነሱ ሀሳቦችን ትኩረት ሰጥቶ በመስራት እንደ ሀገር የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የዴሞክራሲ ባህልን ለመገንባት ሊተጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሥልጠናው የዴሞክራሲ ተቋማት በሀገረ መንግስት ግንባታ የነበራቸውን ሚና በመዳሰስ ተጨማሪ ግብዓት በመውሰድ ተናቦና ተግባብቶ ለመስራት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።