Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የአከራይና ተከራይ ህጋዊ ውል ምዝገባ የፊታችን ሰኔ ይጀመራል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የአከራይና ተከራይ ህጋዊ ውል ምዝገባ ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጀመር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ በሀገሪቱ ያለውን የቤት ኪራይ ችግር ለመፍታት እንዲሁም ፍትሃዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማህበረሰቡ ኑሮና በአጠቃላይ ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚፈጥረውን ጫና ከግምት በማስገባት ተዘጋጅቶ መጽደቁ ይታወቃል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በአዋጁ አስፈላጊነትና አተገባበር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

የቢሮው ኃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ ከተማ አስተዳደሩ አዋጁን በመመሪያ በማስደገፍ ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅቶቹን እያጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህን ተከትሎ ከሰኔ 1 እስከ 30/2016 ዓ.ም በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የግል ቤት አከራዮች ከተከራዮቻቸው ጋር ህጋዊ ሰነዶቻቸውን ይዘው በመቅረብ ምዝገባ ማድረግ አንደሚችሉ ተናግረዋል።

ለምዝገባው የሚያስፈልገውን የሰው ሃይልና መሰረተ ልማት በማደራጀት በኩል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል ።

ቤት አከራዮች ህጋዊ የምዝገባ ውል ለመፈጸም ወደ ወረዳ ጽህፈት ቤቶች በሚሄዱበት ወቅት ቤቱ የራሳቸው ስለመሆኑ ወይንም ህጋዊ ተወካይ መሆናቸውን የሚገልጽ ሰነድ ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል ተብሏል።

ተከራዮች በበኩላቸው ÷ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ወይንም ሌላ ህጋዊ ማንነታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ይዘው መቅረብ እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

በስራ ሰዓት መመዘግብ የማይችሉ አከራይና ተከራዮች ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም በስራ ቀን ማታ ከ12 ሰዓት በኋላ ህጋዊ የውል ምዝገባውን መፈጸም ይችላሉ መባሉን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በምዝገባውና አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ቅሬታዎችን በመቀበል ማስተናገድ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱም ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.