Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያና በኮሪያ ሪፐብሊክ መካከል በትምህርት ዘርፍ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ መካከል በትምህርት ዕድል፣ በከፍተኛ ትምህርት ልምድ ልውውጥ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዙሪያ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ምክክር መደረጉ ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው በኮሪያ ሪፐብሊክ ያላቸውን ቆይታ በተመለከተ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ ከኮሪያ ሪፐብሊክ ልምድ የሚወሰድባቸው ጉብኝቶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።

ከደቡብ ኮሪያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ትምህርት ሚኒስትር ሊ ጁ ሆ ጋር በነበራቸው ውይይትም በሀገራቱ መካከል በትምህርት ዘርፍ ትብብር ዙሪያ መምከራቸውን የገለጹት ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፤ በዘርፉ ያሉ ትብብሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በዚህም በትምህርት ዕድል፣ በከፍተኛ ትምህርት ልምድ ልውውጥ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዙሪያ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ምክክር መደረጉ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስን በሚመለከት የልምድ ልውውጥ ለማድረግና የቴክኖሎጂውን እውቀትና ክህሎቱን ተግባር ላይ ማዋል እንደሚቻል ውይይት ተደርጓል፡፡

የሀገራቱ የትብብር ግንኙነት ቀደም ያለ እና ብዙ የጋራ ታሪክ የነበረው የደም ዋጋ የተከፈለበት በመሆኑ በልዩ መልኩ የሚታይ መሆኑም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡

በዚህም ሀገራቱ በዘርፉ ያላቸውን የትብብር ግንኙነት እና በሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የሚደረጉ ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።

በአመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.