የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዓለም አቀፍ ኦዲት ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዓለም አቀፍ ኦዲት በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡
በዓለም ዓቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት /አይሲኤኦ/ የኦዲት ባለሙያዎች የሚካሄደው ይህ ኦዲት ከ12 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ ነው።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የሲቪል አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሲሳይ ቶላ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ከዓለም ዓቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ተቋም ጋር አብሮ በመስራት ረጅም ዓመታትን አሳልፋለች።
ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ዘርፍን ለማሳደግ በፈረንጆቹ 1944 በ52 ሀገራት መካከል የተፈረመውን የቺካጎ ስምምነት በመፈረም ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ናት በማለት ገልጸው፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ለዘርፉ ማደግ ከድርጅቱ ጋር በትብብር እየሰራች እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ደህንነትን ከብሔራዊ ደህንነት ጋር አጣምራ እንደምታየው በማንሳት፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የሌሎች አየር መንገዶች በረራና የሁሉንም የሀገሪቱን አየር ማረፊያዎችን ደህነንት ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በአማካኝ በዓመት ከ10 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን እና ከ700 ሺህ ቶን በላይ የካርጎ ጭነት የሚያጓጉዘውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደኅንነት ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከ2 ሺህ በላይ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማሰማራት የኢንዱስትሪውን ደህንነት ለማስጠበቅ እየተሰራች እንደሆነ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለአቪዬሽን ደህንነት መጠበቅ ከአየር ማረፊያዎች፣ ከአየር መንገዶች ጸጥታ እና ደህንነት አካላት ጋር የተጠናከረ ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል።
ለዚህም ከተለያዩ ዓለም ዓቀፍ የደህንነት አረጋጋጭ አካላት ጋር ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውም ነው የተጠቆመው።
ይህ ኦዲትም አሁን ያለንበት ደረጃ በመገምገም መልካሞቹን ለማጠናከርና ደካማዎቹን ለማሻሻል እንደሚያስችል ተነስቷል።
የአቪዬሽን ደህንነት ስጋት በየጊዜው መልኩን እየለዋወጠ የሚሄድ በመሆኑ ይሄን የሚመጥን ስራ መስራት ይገባል ተብሏል።
በምስክር ስናፍቅ