በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል አትሌት ለሜቻ ግርማ የዓመቱን የዓለም ፈጣን ሠዓት በማስመዝገብ አሸነፈ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በስዊድን በተካሄደ የዳይመንድ ሊግ የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት አትሌት ለሜቻ ግርማ የዓመቱን የዓለም ፈጣን ሠዓት በማስመዝገብ አሸነፈ፡፡
በዚህም መሠረት በ3 ሺህ ሜትር መሠናክል የወንዶች ውድድር አትሌት ለሜቻ ግርማ 8 ደቂቃ ከ1 ሰከንድ ከ63 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ሲያሸንፍ÷ ሳሙኤል ፍሬው 8 ደቂቃ ከ5 ሰከንድ ከ78 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቅቋል፡፡
በዚሁ ውድድር አትሌት ጌትነት ዋሌ 8 ደቂቃ ከ10 ሰከንድ ከ73 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት አራተኛ እንዲሁም ሳሙኤል ዱጉና 8 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ከ49 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት 11ኛ ደረጃ መያዛቸውን የአትሌቲክስ ፌደሬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በ1 ሺህ 500 ሜትር የሴቶች ውድድር አትሌት ብርቄ ኃየሎም 3 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ ከ84 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት አራተኛ ደረጃን መያዟ ተገልጿል፡፡
በ800 ሜትር ሴቶች ውድድር ደግሞ አትሌት ንግስት ጌታቸው 1 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ ከ77 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት አራተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ጨርሳለች፡፡