የነቀምቴ-ቡሬ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ዳግም ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የነቀምቴ-ቡሬ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ዳግም መጀመሩ ተገለፀ፡፡
የምስራቅ ወለጋ ዞን የመንገድ እና ሎጀስቲክስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ስንበቶ ኢማና÷ የመንገዱ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለህዝብ አገልግሎት እንዲውል እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
የመንገዱ ግንባታ በሦስት ኮንትራት ተከፋፍሎ እየተሰራ መሆኑም ገልፀው ፤ይህም ከነቀምት – አንገር አንዶዴ፣ ከአንዶዴ – አገምሳ እና ከአገምሳ – ቡሬ ሲሆን ከአንዶዴ – አገምሳ እና ከአገምሳ ቡሬ ያለው ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተጠቁሟል።
ከነቀምት-አንገር አንዶዴ ያለውን የመንገድ ግንባታም በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት እንዳሉት ÷ የፕሮጀክቱ ዳግም መጀመር መንግስት የህዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፡፡
የመንገዱ መጠናቀቅ ነፍሰ ጡር እናቶች ወደ ጤና ተቋም እንዲደርሱ እንዲሁም የአካባቢው አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡ እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝላቸው ጠቁመዋል።