አዲስ አበባን ወክለው አጀንዳ የሚሰጡ ባለድርሻ አካላት በአጀንዳቸው ላይ እየመከሩ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባን ወክለው አጀንዳ የሚሰጡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአጀንዳቸው ላይ እየመከሩ ነው፡፡
ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተጀመረው የምክክር ምዕራፍ የወረዳ የህብረተሰብ ተወካዮች ለተከታታይ ሦስት ቀናት ሲያደርጉት የነበረው ውይይት በትናንትናው እለት ተጠናቋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተቋማትና የማህበራት ተወካዮች፣ የህብረተሰብ ወኪሎች፣ ሦስቱ የመንግስት አካላት ተወካዮች፣ የተፅዕኖ ፈጣሪ ተወካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በምክክሩ ተሳትፈዋል።
ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮቻቸውንም እንደሚመርጡ ተገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት አዲስ አበባን ወክለው አጀንዳ የሚሰጡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በከተማ ደረጃ አጀንዳቸው ላይ ምክክር የሚያደርጉ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሀገር አቀፍ የምክክር ሂደት ትናንት መጀመሩ ይታወቃል።