Fana: At a Speed of Life!

የሐረር ከተማን ዘመናዊ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ -አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረር ከተማን ዘመናዊ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት ሀረር ከተማን የሚያዘምኑ የቴክኖሎጂ ስርዓቶች እና መሰረተ ልማቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

ለዚህም ከኢትዮዽያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር በቅንጅት የሚሰራው የዲጂታል የአድራሻ ስርዓት÷ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን ለማሳለጥ፣ የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር፣ በአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት፣ ለዘመናዊ ገቢ አሰባሰብ እና ለንግድ ፈቃድ አሰጣጥ፣ ለአምቡላንስ እና እሳት አደጋ አገልግሎት መሻሻል ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ አንስተዋል።

በተጨማሪም ሐረር ከተማ ያላትን የቱሪዝም ሃብት የምታስተዋውቅበት ስማርት ሲቲ ቱሪዝም መተግበሪያ እና የቋንቋ መተርጎሚያ ሶፍትዌር ማበልፅግ መቻሉን ጠቅሰው ይህም ጎብኚው ባለበት ሆኖ በቀላሉ መረጃ እንዲያገኝ ያስችላል ነው ያሉት።

በሌላ በኩልም ከአጂፕ እስከ ደከር የሚሰራው ፕሮጀከት የመኪና፣ የሳይክል እና የእግረኛ መንገዶችን የያዘ የስማርት ሞቢሊቲ ጽንሰ ሀሳብን ማእከል ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የደህንነት ካሜራ መሰረተ ልማት ቴክኖሎጂ የዜጎችን ደህንነት እና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እና ሐረርን ተመራጭ የቱሪስት መዳራሻ ለማድረግ የሰነቅነውን ራዕይ እውን ለማድረግ እገዛ ያደርጋል ሲሉም አክለዋል።

የመሬት ይዞታን በካዳስተር ስርዓት መመዝገብ መሬት አስተዳደርን ለማዘመንና ከመሬት ጋር የተያያዙ ብልሹ አሰራሮችን እንዲሁም የመሬት ወረራን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

የውሃ መጠን መቆጣጠሪያ ስካዳ እና ቴሌሜትሪ እንዲሁም በየተቋሙ እየተሰሩ ያሉ አውቶሜሽን ስራዎችም ሐረርን ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት እንደሆኑ መግለፃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.