የምርት ዘመኑ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት አበረታች መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምርት ዘመኑ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት አበረታች መሆኑን የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ ገለጹ፡፡
መንግስት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፈር ማዳበሪያን በኬንያ ላሙ በኩል ማስገባት መጀመሯን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር የተቀናጀ የኢንስፔክሽን ቡድን በክልሎች ያለውን የዘንድሮውን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ለመቃኘት በተደረገ የመስክ ምልከታ ግብረ-መልስ ላይ ውይይት ተካሂዷል።
ከግንቦት 15 እስከ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በሰባት ክልሎች የመስክ ምልከታ መደረጉን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮው ዓመት የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ቀድሞ መፈጸሙና ወደ ዩኒየኖችና የኅብረት ስራ ማኅበራት መሰራጨቱ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑም አስረድተዋል፡፡
የምርት ዘመኑ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት አበረታች ነው፤ መንግስት በሰራው የተጠናከረ ስራም ህገ-ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ዝውውር ላይ ትልቅ ለውጥ ታይቷል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የግብርና ሚንስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ባለፈው የምርት ዘመን በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በመረዳትና ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት በዘንድሮው የምርት ዘመን የተሻለ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
የግብርና ኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሣ (ዶ/ር)÷ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የአፈር ማዳበሪያ ጭነው የገቡ ተሽከርካሪዎች ጭነታቸውን አራግፈው በመመለስ ቀሪ የአፈር ማዳበሪያውን ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያጓጉዙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡