በመዲናዋ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት የተቀናጀ ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት የተቀናጀ ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በመቀናጀት እየተፈጠረ ያለውን ሰው ሰራሽ እጥረት ለመፍታት የሚያስችል የተጠናከረ ክትትል ማድረግ ጀምረዋል።
በዛሬው ዕለትም የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የሚኒስቴሩ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች ከፍተኛ መጨናነቅ ባለባቸው አካባቢዎች በመገኘት የትራንስፖርት አገልግሎቱን የማሳለጥ ስራ ሰርተዋል።
በዚህም ውጤታማ ስራ መሥራት መቻሉን ያመለከተው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር መረጃ፤ ክትትሉ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁሟል።
በተደረገው ክትትል ተሽከርካሪዎች ሳይጭኑ ባዶአቸውን እንዳይወጡ፣ አምሽተው ከታሪፍ በላይ ለመጫን እንዳይጠባበቁ እንዲሁም ተገልጋዮች ያሉትን አማራጮች ሁሉ ተጠቅመው እንዲሳፈሩ መደረጉ ተገልጿል።
የተቀናጀ ሥራው በቀጣይነት የሚከናወን ሲሆን፤ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በመስራት ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑም ተነግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከተማ በስራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት ዜጎች ላይ የሚደርሰው መንገላታት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠው አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።