በነ ዮሐንስ ቧያለውና ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) መዝገብ የቀረበውን አቤቱታ ማረሚያ ቤቱ እንዲያስተካክል ታዘዘ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በነ ዮሐንስ ቧያለው እና ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) መዝገብ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር የቀረበ አቤቱታን ተከትሎ ማረሚያ ቤቱ ማስተካከያ እንዲያደርግ ታዘዘ።
ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ህገ-መንግስታዊና በህገ-መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ነው።
በሽብር ወንጀል ተከሰው በቃሊቲና ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኙት ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ተፈጽሞብናል በማለት ያቀረቡትን የሰብዓዊ መብት አያያዝ አቤቱታ መነሻ ማረሚያ ቤቱ ዛሬ ለፍርድ ቤት መልስ ሰጥቷል።
ባለፈው ቀጠሮ በተከሳሾች ከቀረቡ አቤቱታዎች መካከል ቃሊቲ ማረሚያ ቤትን በሚመለከት በግላቸው መታከም የሚፈልጉ ታራሚዎች ህክምና መከልከላቸውን፣ ከቤተሰብ ምግብ የሚቀርብላቸው ታራሚዎች በተፈለገ ሰዓት ምግብ እየቀረበላቸው አለመሆኑን፣ በተጨማሪም ከቤተሰብ ጥየቃ ሰዓት ከሌሎች ታራሚዎች በተለየ አድሎ ይደረግብናል የሚል አቤቱታ አቅርበው ነበር።
በተጨማሪም በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በሴቶች ማረሚያ ቤት መስከረም አበራና ገነት አስማማው የተባሉ ተከሳሾች ለብቻቸው መታሰራቸው እና በታሰሩበት ክፍል ውስጥ ቀን ላይ ከውጭ በር ተዘግቶባቸው እንደሚቆዩ ተጠቅሶ አቤቱታ የቀረበ ሲሆን የቤተመጽሀፍ አገልግሎትን በሚመለከት ነጻነታችንን በሚጋፋ መልኩ እንድንድንገለገል ተደርገናል የሚሉ አቤቱታዎች ተያይዘው ቀርበው ነበር።
በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ደግሞ በነ ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) መዝገብ የተለያዩ መጽሄቶች እንዳይገቡ፣ ውክልና ለመስጠትና ገንዘብ ለቤተሰብ በባንክ ለመላክ ተከልክለናል ባሉ ተከሳሾች የቀረበ አቤቱታ መኖሩን ፍርድ ቤተ ተመልክቷል።
በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ በግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ በሰጠው ትዕዛዝ፤ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው መኮንን እና የማረሚያ ቤቱ የሴቶች ማህበራዊና ማረፊያ ማዕከል ኃላፊ ኮማንደር አይናለም ሳህሉ እንዲሁም ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የፍትህ አስተዳደር አስተባባሪ ተወካይ ኮማንደር ኢብራሂም አህመድ ችሎት ቀርበው መልስ ሰጥተዋል።
ኮማንደር አስቻለው አቤት ባዮቹ ጥቃት እንዳይደርስ ለመከላከል ታሳቢ ያደረገ ጥበቃ ይደረግላቸዋል እንጂ ከሌሎች በተለየ አድሎ አልተደረገባቸውም በማለት መልስ ሰጥተዋል።
የቀጠሮ እስረኞችን ከፍርደኞች ጋር እንዲታሰሩ መደረጉን በሚመለከት ለቀረበው አቤቱታ በቦታ ጥበት ምክንያት የተከሰተ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ማስተካካያ መደረጉን ገልጸው መልስ ሰጥተዋል።
ምግብን በሚመለከት ከመደበኛው ቀን ተጨማሪ ቀናቶች ምግብ እንዲገባላቸው ማስተካከያ መደረጉን እንዲሁም ከጥየቃ ጋር በተያያዘ ማንነታቸው በማይታወቁ ሰዎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል የተደረገ እንጂ ታራሚዎችን ለይተን እንዳይጠየቁ ለማድረግ አደለም ብለዋል።
ህክምናንም በተመለከተ ለማንኛውም ታራሚ በተቋሙ አሰራር መሰረት ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል ከተቋሙ በላይ ሲሆን ሪፈር ሲጻፍ ደግሞ በውጪ እንዲታከሙ የሚደረግበት አሰራር መኖሩን ጠቅሰው መልስ ሰጥተዋል።
ማረሚያ ቤቱ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንደሚያከብር ገልጸው፤ በተነሱ አቤቱታዎች ላይ ማረሚያ ቤቱ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ሴቶች ታራሚዎችን በሚመለከት መልስ የሰጡት ኮማንደር አይናለም፤ የታራሚዎች ክፍል ከውጭ እንደማይዘጋ ገልጸዋል።
በወንድ እንድንፈተሽ ተደርገናል ለሚለው አቤቱታ ደግሞ ወንድ ብቻውን ሳይሆን ከሴት ፈታሽ ጋር በመሆን ለቁጥጥር ተቀላቅሎ መግባቱን ጠቅሰው፤ ለዚህም በአሁን ወቅት ማንም ወንድ ሴቶች ማረሚያ እንዳይገባና በሴት ብቻ እንዲፈተሽ መደረጉን ተናግረዋል።
ቤተመጽሐፍትን በሚመለከት የማንበቢያ በር ላይ ብቻ ጥበቃ እንደሚቀመጥ ገልጸው፤ ይህም ለታራሚዎች ደህንነት በማሰብ የተሰራ ስራ መሆኑን ጠቅሰው መልስ ሰጥተዋል።
የውበት አጠባበቅ ላይ በተገቢው እንዲጠቀሙ መደረጉን ጠቅሰው፤ በሴቶች ማረሚያ ቤት የማስተካከያ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ቂሊንጦ ማረሚያ ቤትን በሚመለከት የጎላ ክፍተት እንደሌለና በጠበቆች በኩል ምስጋና የቀረበ ቢሆንም አንዳንድ ታራሚዎች ለቤተሰብ ገንዘብ በባንክ ለመላክና ውክልና ለመስጠት የሚቀርቡ ጥያቄዎች ፈጥነው አልተተገበሩም ለሚለው አቤቱታ መልስ የሰጡት ተወካዩ ኮማንደር ኢብራሂም፤ አፈጻጻም ላይ ለተነሳው አቤቱታ በአፋጣኝ ምላሽ እንሰጣለን ብለዋል።
የተሰጠውን ምላሽ የተከታተለው ፍርድ ቤቱ ተገቢ ማስተካከያ እንዲደረግና ታራሚዎች መካከል ልዩነት ሳይደረግ በቅንነት የሰብዓዊ መብት አገልግሎት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ትዕዛዝ ሰጥቶ፤ በቀጣይ በሚኖር ቀጠሮ አፈጻጸሙ ላይ ለውጥ ካለ እንደሚመለከትና ካልተተገበረ ደግሞ አስፈላጊውን ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ገልጿል።
በታሪክ አዱኛ