እናቱን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ግለሰብ በሞት እንዲቀጣ ተወሰነ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እናቱን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ግለሰብ በሞት ፍርድ እንዲቀጣ የአዳማ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዉሳኔ አሳለፈ።
በአዳማ ከተማ ቦሌ ክፍል ከተማ በተለምዶ ደካ አዲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም እናቱን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ተከሳሽ ቶሎሳ ውይም ፍቅሩ አሸናፊ ላይ የአዳማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት ውሳኔ አሳልፏል።
ተከሳሹ እናቱን በስለት (ቢላዋ) በአሰቃቂ ሁኔታ ወግቶ ህይወታቸውን እንዲያጡ አድርጓል።
ተከሳሹ ድርጊቱን የፈጸመው በቁማር የተበላዉን ገንዘብ እናቱ ያላቸውን ንብረት በመሸጥ እንዲተኩለት ለማድረግ ሲል እየደበደበ ያሰቃያቸው እንደነበር ዐቃቤ ሕግ በማስረጃ አረጋግጧል።
በዚህ ብቻ ያላበቃው ተከሳሽ ሚያዚያ 21 ጠዋት በአሰቃቂ ሁኔታ የእናቱ ህይወት እንዲያልፍ አድርጓል በሚል ከባድ የግድያ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።
በዚህም ተከሳሹ የቀረበበትን ከባድ የወንጀል ድርጊት ማስተባበል ባለመቻሉ በሞት እንዲቀጣ ችሎቱ ውሳኔ አሳልፏል።
በተከሳሹ ላይ የተጣለው የሞት ፍርድ በአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሲጸድቅ ተፈጻሚ ይሆናል።
በኦልያድ በዳኔ እና በአብደላ አማን