ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከጋቪ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በስዊዘርላንድ ጀኔቫ እየተካሄደ ባለዉ 77ኛዉ የአለም ጤና ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ያሉት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከግሎባል የክትባት ህብረት ኢኒሽዬቲቭ (ጋቪ) ጋቪ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሳኒያ ኒሽተር ጋር መክረዋል፡፡
በውይይታቸውም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በኢትዮጵያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ገለጻ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጻ አድርገዋል።
በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ ፕሮግራሞች ክትባት ለዜጎች ተደራሽ እንዲሆን የመንግስትን ጥረት በማገዝ በኩል የጋቪና ሌሎች አጋር ድርጅቶች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት፣ የእናቶችና የህጻናት ሞት እንዲቀንስ ክትባትን ተደራሽ በማድረግ ሰፊ ስራዎች እንደተሰሩ ተናግረዋል፡፡
ሁሉምን አይነት ክትባት በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ የግብአት እጥረት መኖሩን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ጥራቱ የተረጋገጠ ፍትኃዊ የክትባት አቅርቦትና ስርጭት እንዲኖር ጋቪ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ዶ/ር ሳኒያ በበኩላቸው ጋቪ ለኢትዮጵያ የሚያደርገዉን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።