ፕሬዚዳንት ባይደን ዩክሬን የሩሲያን ኢላማዎች በአሜሪካ የጦር መሳሪያ እንድትመታ ፍቃድ መስጠታቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን በካርኪቭ ግዛት አቅራቢያ የሚገኙ የሩሲያን ኢላማዎች አሜሪካ ባቀረበችው የጦር መሳሪያ እንድትመታ ፍቃድ መስጠታቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የሩሲያ ጦር በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በድንበር አቅራቢያ በሚገኘው አካባቢ ላይ ባደረገው ድንገተኛ የማጥቃት ዘመቻ በካርኪቭ ግዛት ከፍተኛ ድል ማስመዝገቡ ተመላክቷል።
ከካርኪቭ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ የመኖሪያ ህንፃ ላይ በሩሲያ በተፈጸመ ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 16 መቁሰላቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
አሜሪካ በሩሲያ ውስጥ የረዥም ርቀት ጥቃቶችን ከመከልከል ጋር በተያያዘ ያላት የወታደራዊ ታክቲካል ሚሳኤል ስርዓት ፖሊሲ አለመለወጡን ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።
አዲሱ ፖሊሲ የሩስያ አውሮፕላኖችን ማጥቃትን ይጨምር እንደሆን የተጠየቁት ባለስልጣኑ÷ ዩክሬናውያን ሊያጠቃቸው የመጣን አውሮፕላን በሩሲያ ምድርም ቢሆን እንዳይመቱ ተከልክለው አያውቁም ሲሉ ነው የገለፁት።
ይሁን እንጂ እስከ አሁን ከሁዋይት ሀውስ በኩል የተሰጠ አፋጣኝ አስተያየት አለመኖሩን ቢቢሲ ዘግቧል።
ዩክሬን ከምዕራቡ ዓለም የሚቀርብ የጦር መሳሪያ መጠቀም የምትችልበትን ገደብ ለማቃለል እንግሊዝ በሯን ክፍት ማድረጓን ቀደም ሲል አሳውቃለች።
ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቱ ሂደት ግጭቱን የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋት ቢኖርም÷ በርካታ የአውሮፓ መሪዎችም የጦር መሣሪያ አጠቃቀም ላይ የተቀመጡ እገዳዎች ቀለል እንዲሉ ጠይቀዋል።