ዩኒሴፍ ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጋር በትብብር የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ፡፡
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ከዓለም አቀፍ የዩኒሴፍ የህጻናት ጥበቃ ዳይሬክተር ሸማ ሰን ጉፕታ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ ኮሚሽኑ የቀድሞ ተዋጊዎች ዲሞቢላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም አፈፃፀም፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ቀጣይ የስራ እቅዶችን በተመለከተ ኮሚሽነር ተመስገን ገለጻ አድርገዋል።
በተጨማሪም ዩኒሴፍ ከዚህ በፊት ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ ላደረጋቸው ድጋፎች አመስግነው÷ በቀጣይ ፕሮግራሙና ፕሮጀክቶች በታቀደዉ መሰረት እንዲሳካ ትብብሩና ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ሸማ ሰን ጉፕታ÷ ኮሚሽኑ ተልዕኮዉን ለመወጣት በያዘው ፕሮግራም ቅድሚያ የሚሰጣቸውንና ልዩ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተጎጂ፣ ወጣት ሴትና ወንድ የቀድሞ ተዋጊዎችን ታሳቢ አድርጎ እየሰራ መሆኑን አድንቀዋል።
በቀጣይም ዩኒሴፍ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን መግለጻቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በተጨማሪም ፕሮግራሙ በስኬት እንዲከናወን ዩኒሴፍ በተለይ በዘላቂነት የማቋቋም ድጋፍ ላይ ትኩረት በማድረግ ኮሚሽኑ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዳይሬክተሯ አረጋግጠዋል።