በክልሉ በዘንድሮው ክረምት በ32 አካባቢዎች 460 ሺህ ሰዎች፣ 280 ሺህ እንስሳት እና 15 ሺህ መኖሪያ ቤቶች የጎርፍ አደጋ ሥጋት እንዳለባቸው በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ ገልጸዋል።
ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ከሆኑት ውስጥም 15 ሺህ ሰዎች ለሚኖሩባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰው፤ በወቅቱ ለማጠናቀቅም እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
እንደ ድርቅ ሁሉ ለጎርፍ አደጋም ትኩረት ተሰጥቶ በመስራት ከክልሉ ወረዳዎች ውስጥ የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸው ተጠንተው መለየታቸውንም ጠቅሰዋል።
ከመንግሥት እና ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ 94 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በጀት ለ20 ተጋላጭ አካባቢዎች የቅድመ መከላከል ሥራዎች በጀት መለቀቁንም አመልክተዋል።
አብዛኞቹ ወረዳዎችም በተለቀቀላቸው በጀት ሥራ እየሠሩ እንዳሉና ያልጀመሩ መኖራቸውንም አቶ ብርሃኑ ጠቅሰው፤ ሥራውን ያልጀመሩትን በጀቱ ተነስቶ እጥረት ላለባቸው እንደሚመደብ አሳውቀዋል።
በብዛት የጎርፍ ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ በጀት የተመደበ መኾኑን እና ማኅበረሰቡም በራሱ ሊሠራቸው የሚችላቸው ሥራዎች መኖራቸውን ዳይሬክተሩ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።