የአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንስ አቅሙን ከ70 ቢሊየን ዶላር በላይ ለማሳደግ የሚያስችለውን ስትራቴጂ ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ በኬንያ ናይሮቢ እያካሄደ ባለው ዓመታዊ ጉባኤ እስከ 2033 የሚተገብርውን አዲስ የ10 ዓመት ስትራቴጂ ይፋ አድርጓል።
ስትራቴጂው የበለጸገች፣ አካታች፣ ተጽእኖን መቋቋም የምትችልና አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካን መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፤ ስትራቴጂው በአህጉሪቱ የሚደረጉ ጫናዎችን በመቋቋም ዘላቂ የምጣኔ ሃብት እድገት ለማምጣት የሚያግዝ ፍኖተ ካርታ እንደሆነም ተገልጿል።
በተመሳሳይ አፍሪካ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል ከግምት ያስገባ ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲና÷ ባንኩ በቀጣይ 10 ዓመታት የሚያደርገው ድጋፍ አህጉሪቱን ለማሸጋገር ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኮቪድ-19 ያስከተለው ዘርፈ ብዙ ተጽእኖ፣ የአየር ንብረት ለወጥ፣ ግጭትና የፖለቲካ አለመረጋጋት አህጉሩን እየፈተኑ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ስትራቴጂው ችግሮችን ለመቋቋም እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
ስትራተጂው ድጋፍ ለማድረግ ባንኩ የሚወስዳቸውን ወሳኝና አስቸኳይ እርምጃዎችን ያስቀመጠ ነው ብለዋል፡፡