Fana: At a Speed of Life!

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ያለገደብ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያለገደብ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ሆነ።

መተግበሪያው በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በቀጥታ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው ተብሏል።

መተግበሪያውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት እና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ እንዳሉት፤ የግድቡ ግንባታ ከተጀምረበት ጊዜ አንስቶ ከ320 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

ከዚህ ባለፈም ለግድቡ የሚሰጠው ብድር 9 በመቶ መድረሱን አመላክተዋል፡፡

አሁን ላይ (Itsmydam.com) የተሰኘውን መተግበሪያ አሻሽሎ በማዘጋጀት ኢትዮጵያውያን ገንዘብ በማዋጣት ሌሎች እንዲያዋጡ ብሎም ድጋፍ የሚያደርጉበት ስርዓት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።

መተግበሪያው ኢትዮ-ዳይሬክት ከተሰኘው መተግበሪያ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ በውጭ የሚገኙ ዜጎች መሳተፍ እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የግድቡ ግንባታ 96 በመቶ መድረሱን ያነሱት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ (ኢ/ር)፤ ግድቡን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ከ40 ቢሊየን ብር በላይ ወይም 850 ሚሊየን ዶላር የሚያስፈልግ መሆኑን አንስተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያውያን ያልተቋረጠ ተሳትፎ ለዚህ ደርሷል ያሉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በማንሳት መተግበሪያውን በመጠቀም የቀረውን ግንባታ ለማጠናቀቅ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ በላይነህ አቅናው የመተግበሪያው ወደ ስራ መግባት ዳያስፖራው በቀጥታ ድጋፍ ማድረግ የሚችልበትን ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው እስከ የካቲት ወር 192 ቢሊየን ብር ወጪ የወጣበት መሆኑን ገልጸው፤ የግድቡ ዋና ዋና ስራዎች በተያዘው አመት እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

በሃይማኖት ኢያሱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.