ለዘላቂ ሰላም የሀገራዊ ምክክር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገር ስትመክር ስንጥቃቷ ይሞላል፤ የተጣመመው ይቃናል፤ ልብ ያዘለው ቂም በንግግር ይፈተሻል፤ ቁርሾውም በይቅርታ ይከስማል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት በዘርፈ ብዙ ችግሮች ያልፋሉ እያለፉም ይገኛሉ፤ ችግሮችን ለማለፍ ደግሞ መፍትሄ የሚሏቸውን እርምጃዎች ይወስዳሉ፡፡
ዓለም ከተስማማባቸው መፍትሄዎች መካከል ደግሞ በቀዳሚነት ሀገራዊ ምክክር ማድረግ ነው፡፡
ሀገራዊ ምክክር፥ ሀገራዊ ችግሮችን በመፍታት በመንግስትና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ቡድኖችና ተቋማት መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር የሚያደርግና ዘላቂ የሆነ ሰላምን አስጠብቆ በምክክር የጸናች ሀገርን ያስቀጥላል።
በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሀገራት ምክክር የተደረገ ሲሆን፥ በተለይም ሀገር ከፍተኛ የሆነ ችግር ውስጥ ስትገባ ተቀዳሚውና አዋጭ የሆነውን ሀገራዊ ምክክር በመተግበር ወደ አንድ መፍትሄ ለመምጣት ያስቻላቸው ብዙ ናቸው፡፡
ደቡብ አፍሪካ፣ ታይላንድ፣ ጋቦን፣ ሊባኖስ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬኒያ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዝያ እና ሌሎች ሀገራት ሃሳቦቻቸውን ቅራኔዎቻቸውን ጠረጴዛ ላይ በማስቀመጥ መክረዋል፤ ይበጀናል ያሉትንም ወስደዋል፡፡
ሰላም እንዳይታወክ ፍትህ መረጋገጥ አለበት፤ ቅራኔዎች በጠብመንጃና በኃይል፤ ሃሳብም በጦር ሳይሆን በምክክርና በይቅርታ ሊታከሙ ይገባል።
ግለሰብ እንደግለሰብ፣ ህዝብ እንደህዝብ መንግስት እንደ መንግስት ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡
በዚህ ወቅትም ሃሳብ ቀዳሚውን ስፍራ ሲወስድ፥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በማክበር መምከር ነገ በአፈሙዝ የሚጠፋውን ዜጋ መታደግ፣ ለጦርነት የሚወጣውን መዋዕለ ንዋይ ለልማት ለማዋል ሀገር እንድትቀጥል ሰፊውን ድርሻ ይወጣል፡፡
በዚህም ስኬታማ የሆነ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግና የግጭት መንስኤዎችን ለመፍታት እንዲሁም የውይይቱን አቅም ከፍ ለማድረግ መንግስትና የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ ሊሆን እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአሜሪካ የሰላም ኢንስቲትዩት ይገልጻሉ፡፡
በመቀጠልም ምክክሩ ግልጸኝነትና የህዝብን ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል፤ በመድረኩ ውስጥ ከሚኖሩት ተወካዮች ባሻገር ውይይቱ ሰፊውን ህዝብ የሚያጠቃልልበት ዘዴም ሊኖረው ይገባልም ይላል ኢንስቲትዩቱ።
ምክክሩ ሁሉንም በእኩል በመመልከት ሃሳብን በነጻነት እንዲያንሸራሽሩ እድል መስጠት እንደሚገባም ይጠቀሳል፡፡
የግጭት መንስኤዎችን የሚዳስስ አጀንዳ በማስቀመጥ ምክክሩ በአንድ ሀገር ውስጥ ባሉ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡
እንደ አብነትም እንደዜጋ የሚሰጡ መብቶች፣ የምርጫ ሂደቶች፣ የመንግስት መዋቅርና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ በግልጽ በመምከር ለተግበራዊነቱ ስምምነት ማድረግ ያስፈልጋል ያለው ኢንስቲትዩቱ፥ ይህ ካልሆነ ግን ምክክር ማድረጉ ጉንጭ አልፋ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ እየመከረች ነው፡፡ ምክክሩ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣና ከጠብመንጃ የሃሳብ የበላይነትን በመቀበል ኢትዮጵያ እያለፈችበት ላለው ችግር መፍትሄ ያመጣል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
በመሰረት አወቀ