Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ያለው ሰላም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሥራታችን የተገኘ ነው- አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል ያለው ሠላም የተገኘው በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት በመሥራታችን የተገኘ ነው ሲሉ ርዕሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡

በልሉ የሚገኙ እና በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከርዕሰ መሥተዳድሩ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ ደስታ በውይይቱ ላይ እንዳሉት÷ በክልሉ ያለው ሰላም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሰራቱ የተገኘ ነው።

በክልሉ ያለው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው እንዲሁም ልማትና መልካም አሥተዳደርን ለማስፈን ቅንጅታዊ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

የመድረኩ ዋና ዓላማም በክልሉ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠልና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ነው ማለታቸውን የርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

የክልሉ መንግሥት በሚያከናውነው ሥራ የሚታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማበረታታት ጉድለቶች ሲኖሩም በመነጋገር በጋራ የመሥራት ባህልን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ ሐሳብ ቢኖራቸውም÷ በሀገርና በክልል ሰላም፣ ልማትና አንድነት ላይ በጋራ መንቀሳቀስ እንሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.