Fana: At a Speed of Life!

የአለም የደም ለጋሾች ቀን  እየተከበረ ነዉ

አዲስ አበባ፣ሰኔ 7፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአለም የደም ለጋሾች ቀን  “ ደም በመለገስ አለማችንን የበለጠ ጤናማ ያድርጉ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነዉ ፡፡

የአለም የደም ለጋሾች ቀን በአለም ፣ በኢትዮጵያም ለ17ተኛ ጊዜ እየተከበረ ነዉ።

በየአመቱ ሰኔ 7 የሚከበዉ ይህንኑ እለት የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎትም የማይተካዉን የህይወት ስጦታ የሚሰጡትን በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን ለማመስገንና ሌሎች ሰዎችም መደበኛ ደም ለጋሽ በመሆን ህይወትን እንዲታደጉ ለማበረታታት  እያከበረ ይገኛል፡፡

ዕለቱን በማስመለክት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ባስተላለፉት መልዕክት÷ዛሬ በአለማችንንና በሀገራችን ለ17ኛ ጊዜ እየተከበረ ለሚገኘው የአለም ደም ለጋሾች ቀን በሀገሪቱ ለሚገኙ ሁሉም በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

ሚኒስትሯ አያይዘውም ደም በመለገስ ህይወትን ለማዳን ለምትሰጡት ውድ ስጦታ ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽን በሃገራችን መከሰቱን ተከትሎ የተፈጠረውን የደም ክምችት እጥረት ለመቅረፍ ላሳያችሁት ትብብርና ለጥሪያችን ለሰጣችሁት ፈጣን ምላሽ በደም ተጠቃሚ ታካሚዎች ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁም ነው ያሉት፡፡

ከደም ማሰባሰብ መመርመርና ደህንነቱ የተረጋገጠ ደም ለጤና ተቋማት በወቅቱ እንዲደርስ ለምትሰሩና በሁሉም የሃገራችን ደም ባንኮች የምትገኙ ባለሙያዎችንም አመሰግናለሁ ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡

አያይዘውም አሁንም ሁላችሁም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጋችሁ በመደበኛነት ደም በመለገስ በዚህ ወረርሽኝ ወቅትም ደም የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ተገቢውን የደም አቅርቦትና ህክምና እንዲያገኙ እንድትረዱ እጠይቃለሁ ብለዋል፡፡

 

የብሄራዊ ደም ባክን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ያረጋል ባንቴ እለቱን አስመልክተዉ በሰጡት መግለጫ ÷ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከተሰተበት በዚህ ወቅት ደህንቱ የተረጋገጠ እና በቂ ደም ማሰባሰብና ማቅረብ በአለም አቀፍ ደረጃ አደጋ ከተጋረጠባቸዉ ስራዎች ዉስጥ አንዱ ነዉ ብለዋል ።

በሽታን ለመከላከል በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት የደም ልገሳ መርሀግብሮች በመሰረዛቸዉ ወደ ደም ባንክ የሚመጡ ለጋሾች በለመኖራቸዉ በአለም አቀፍ ደረጃ ከባድ የደም እጥረት ፈጥሯልም ነዉ ያሉት ፡፡

በኢትዮጵያም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የደም ለጋሾች ቁጥር ማነስ ታይቶ ነበር ያሉት አቶ ያረጋል ÷ በሀገሪቱ ያሉ የደም ባንኮች ከጤና ሚኒስቴር እና ከክልል ጤና ቢሮዎች  ጋር ባደረጉት የተቀናጀ ስራ ቀና የሆነዉ የደም ለጋሾች መልካም አሳቢነት የታዩ እጥረቶችን በቶሎ መፍታት ተችሏል ብለዋል ፡፡

“በአሁኑ ሰዓትም በሁሉም የደም ባንኮች በቂ የሆነ የደም ክምችት ይገኛል” ብለዋል ።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለዉም “ አሁን ያለዉ የደም ክምችት ከ16ሺህ ዩኒት ደም በላይ ሲሆን ይህም በኮቪድ ወረርሽኝ  የመጀመሪያዉ ወር  ( መጋቢት ) ላይ ከነበረዉ መጠን በ4እጥፍ የሚበልጥ  ሲሆን÷ ከዚህ ዉስጥ 6ሺህ ዩኒት ደም ክምችት ያለዉ በአዲስ አበባ ነዉ፡፡” ብለዋል ፡፡

አሁን ላይ ምንም አይነት የደም እጥረት የለም ያሉት የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ይሁን እንጂ   አሁን ያለዉ  የደም ክምችትም  የአምስት ሳምንት ፍጆታ ነውም ነው ያሉት።

ለአብነትም በአዲስ አበባ ብቻ በሳምንት ከ1ሺህ በላይ ዩኒት ደም ያስፈልጋል ሲሉ  ዜጎች የማይቋረጥ የደም ልገሳን እንዲያከናዉኑና  “ ለግሰዉ የማያዉቁትም ዛሬ ቢጀምሩ በመስጠት ዉስጥ ከሚገኘዉ ደስታ ጥግ ይደርሳሉ ሲሉ” ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

በመላ ሀገሪቱ ያሉ የደም ባንኮችም ወረርሽኙን ለመከላከል የተቀመጡ የጥንቃቄ ስራዎችን በአግባቡ በመተግበር የደም ለጋሾችን እና የሰራተኞቻቸዉን ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተዉ እንደሚያስተናግዱም አቶ ያረጋል ተናግረዋል ፡፡

ሃላፊው አያይዘውም ህይወትን በመታደጉ ሂደት ሁሉ የደም ማሰባሰብን የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች እና ትብብር ለሚያደርጉ ግለሰቦች እና ተቋማትም እለቱን አስመልክተዉ አመስግነዋል ፡፡

በፀጋዬ ወንድወሰን

 

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.