የ4 ዓመት ሕጻንን ያገቱ ግለሰቦች ከ23 እስከ 19 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ የ4 ዓመት ሕጻንን በመሰወር ወንጀል የተከሰሱ 3 ግለሰቦች ከ23 እስከ 19 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ፡፡
ተከሰሾቹ 1ኛ መሳይ ኢተሳ፣ 2ኛ ረድኤት በላቸው እና 3ኛ ያቦነህ ፍቅሬ ይባላሉ፡፡
1ኛ ተከሳሽ በምሁር አክሊል ወረዳ የኮብልስቶን ንጣፍ ስራ በኮንትራት ወስዶ በመስራት ላይ እያለ የሰራውን ስራ ቁጥጥር ከሚያደርገው የፕላን ኮሚሽን መስሪያ ቤት ባለሞያ አሰፋ ተስፋዬ ጋር የስራ ጥራት እና የክፍያ አፈፃፀምን በተመለከተ አለመግባባት ይፈጠራል፡፡
በዚህም በ2015 ዓ.ም በተለያየ ጊዜ ልጁን አግትበታለሁ እያለ ሲዘት ቆይቶ ሚያዝያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 9 ሰዓት የግል ተበዳይን ሕጻን ጠልፈው እንደወሰዱ በክሱ ተመላክቷል፡፡
በወረዳው ሰላም ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 4 ዓመት የሆነውን የግል ተበዳይ ሕጻን ባህራን አሰፋ መኖሪያ ቤታቸው አካባቢ ከሌሎች ሕጻናት ጋር እየተጫወተ እያለ 2ኛ ተከሳሽ አባብላ ወደ ቤቷ በማስገባት 3ኛ ተከሳሽ ወስዶ ለ1ኛ ተከሳሽ እንዳቀበለው በክሱ ተጠቅሷል፡፡
ግለሰቦቹ ሕጻኑን ጠልፈው የወሰዱት በመሆኑ በፈፀሙት በዋና ወንጀል አድራጊነት ለአካለ መጠን ያልደረሰን ልጅ በመጥለፍ ወንጀል ተከሰዋል።
በዚህ መሰረትም የጉራጌ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት 1ኛ ተከሳሽ እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ 23 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
እንዲሁም 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ እያንዳዳቸው በ19 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የክልሉ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡