በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ በአሲዳማነት የተጠቃ መሬትን የማከም ስራ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ በአሲዳማነት የተጎዳ 52 ሺህ 710 ሄክታር መሬት በግብርና ኖራ የማከም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በሚኒስቴሩ የአፈር ኃብት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሊሬ አብዮ እንደገለጹት÷ የአፈር አሲዳማነት የሚያደርሰውን ችግር ለማቃለል አርሶ አደሩን በማሳተፍ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡
በዚህም በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በመመደብ በ52 ሺህ 710 ሄክታር መሬት ላይ በግብርና ኖራ የማከም ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
በበጀት ዓመቱ ክልሎችን ጨምሮ እንደ ሀገር 200ሺህ ሄክታር መሬት በኖራ ለማከም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ሥራው አሁን ላይ በተለያየ የትግበራ ደረጃ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የተቀናጀ የተፈጥሮ ኃብትና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በመሥራት የአፈር ለምነትን ለመጠበቅና አሲዳማነትን ለመከላከል ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል አሲዳማ አፈርን መቋቋም የሚችሉ የሰብል አይነቶችን በመዝራት በምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡