መዲናችንን ተምሳሌት ለማድረግ የጀመርነውን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት ከተማ ለማድረግ የጀመርነውን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ 9ኛውን ከተማ አቀፍ የሳይንስና ፈጠራ የተማሪዎች ዓውደ ርዕይ በወዳጅነት አደባባይ መክፈታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
አውደ ርዕይው “በፈጠራ ስራ የዳበረ ትውልድ ለሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡
“እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ፍሬ እየሰጡ መሆናቸውን በዓውደ ርዕዩ የተመለከትናቸው የተማሪዎች የፈጠራ ስራዎች አስረጂ ናቸው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
“ለትውልድ ግንባታ የላቀ ትኩረት በመስጠት የተማረውን በተግባር የሚያሳይ ችግር ፈቺ ትውልድ ለመገንባት እና አዲስ አበባን ትውልድ የሚገነባበት፣ ለሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና የሚተጉ ጥበበኛ ወጣቶችን የምታፈራ፣ የሀገራችን የብልጽግና ተምሳሌት ከተማ ለማድረግ የጀመርነው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉም አረጋግጠዋል።