ለጋምቤላ ክልል 4 ሺህ 348 መጽሃፍት ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሃፍት አገልግሎት ለጋምቤላ ክልል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ 4 ሺህ 348 የማጣቀሻ እና የፍልስፍና መጽሃፍትን አስረክቧል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ይኩኑአምላክ መዝገቡ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ÷ በእውቀትና ክህሎት የዳበረ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመገንባት የንባብ ባሕልን ማጠናከር ይገባል፡፡
ትውልዱ የማንበብ ክህሎቱን በማዳበር የነገ ሀገር ተረካቢነቱን በመረዳት ትምህርቱን በንቃት መከታተል ይጠበቅበታልም ነው ያሉት።
አብያተ መጽሃፍት የመረጃ አያያዝ ላይ ትኩረት በመስጠት ሊሰሩ እንደሚገባ መናገራቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ኡቦንግ ኡቻላ (ረ/ፕ/ር) በበኩላቸው ÷ በድጋፍ የተገኙት መጽሃፍት በአግባቡ ተይዘው ለታለመላቸው አላማ እዲውሉ ይደረጋል ብለዋል።