ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስራ የእስካሁኑ ሒደት ፈተናዎች እና የቀጣይ እቅዶች ላይ የሚመክር የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ተገኝነተው ‘ቴክኖሎጂ ለሀገር ልማት የሚያመጣው ቱርፋት እና የዲጂታል ኢኮኖሚ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አጀንዳ’ በሚል ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሀሳብ፤ ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
በማንኛውም የመንግስት አገልግሎት ላይ ያለውን ብልሹ አሰራር ለማስተካከል ቴክኖሎጂ የማይተካ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ ማህበራዊ ተሳትፎ እና የስራ እድል ለመፍጠር ጥሩ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ተደራሽነትን በማሳደግ ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ስራ ማስገባት ላይ ከፍተኛ ሚና አለው በማለት ገልጸው፤ ወጣቱ ለቴክኖሎጂ ያለው መሰጠትን በአግባቡ ለመጠቀም መዘጋጀት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ከመንግስት አምስት ትኩረቶች መካከል አንዱ ቴክኖሎጂ መሆኑን ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በ2025 ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት መንግስት ያሳየው ተነሳሽነት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት እንዳለው ማሳያ ነው ብለዋል።
በዚህም እሳቸው የሚመሩት ሶስት ዓላማዎች ያሉት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት መንግስት በማቋቋም ዘርፉን ለማሳደግ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራን እና ምርምርን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በፍሬህይወት ሰፊው