የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን በልብና በካንሰር ሕክምና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን በልብና በካንሰር ሕክምና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
የኮሌጁ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዱዓለም ደነቀ(ፕ/ር) እንደገለጹት ፥ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን በልብና በካንሰር ሕክምና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ሆስፒታሉ የልብና የካንሰር የልህቀት ማዕከል ለመሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው ፥ በቀጣይ ዓመት መስከረም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ መሆኑን ተከትሎ በሚዘረጋው መዋቅር የልህቀት ማዕከላቱ ተቋማዊ ቅርጽ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር ሆስፒታሉን የልብ የልህቀት ማዕከል ለማድረግና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በተለይም በልብ ሕክምና ሰፊ ምርምር በማድረግና ባለሙያዎች በተወሰኑ ዘርፎች እንዲሰለጥኑ በማድረግ ሆስፒታሉን ለማጠናከር ትኩረት ተደርጓልም ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው።
የሕክምና ማዕከሉን አገልግሎት ሊያጠናክሩ የሚያስችሉ ዘመናዊ መሣሪያዎችና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች መገጠማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በተመሳሳይ ሆስፒታሉን የካንሰር ሕክምና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የሕክምና ግብዓት በማሟላት፣ የዘርፉን የሰው ኃይል በማሰልጠንና ሌሎች አስፈላጊ ሥራዎች በመስራት ላለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ነው የገለጹት።
ሆስፒታሉ የልህቀት ማዕከል ሲሆን ፥ ከመደበኛው ሥራ በተጨማሪ ለልብና ለካንሰር ታካሚዎች ከምርመራ እስከ መጨረሻው ድረስ የሚዘልቅ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችልና በሁለቱ ዘርፎች ተጠቃሽ የምርምር ማዕከል ያደርገዋል ብለዋል።