በጋና የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት የተለያዩ ኩባንያዎች እየተፎካከሩ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጋና የመጀመሪያውን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት እስከ ፈረንጆቹ ታህሳስ ወር ድረስ አንድ ኩባንያን እንደምትመርጥ የኢነርጂ ሚኒስቴር ገልጿል።
የፈረንሣይ ኢዲኤፍ፣ መሰረቱን አሜሪካ ያደረገው ኑስካል ፓወር እና ሬግናም ቴክኖሎጂ ግሩፕ እና የቻይና ናሽናል ኒውክሌር ኮርፖሬሽንን ጨምሮ የተለያዩ ኩባንያዎች ግንባታውን ለማካሄድ እየተፎካከሩ ነው፡፡
በሚኒስቴሩ የኒውክሌር እና አማራጭ ኢነርጂ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሮበርት ሶግባጂ እንዳሉት፤ የደቡብ ኮሪያው ኬፕኮ እና በስሩ የሚገኘው የኮሪያ ሀይድሮ ኒውክሌር ኃይል ኮርፖሬሽን እንዲሁም የሩሲያው ሮሳቶም ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት የሚቆየውን ውል ለመፈረም ይወዳደራሉ ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
በካቢኔው በሚፀድቀው የመጨረሻ ምርጫ÷ በሚቀርበው የገንዘብ ሞዴል እና በዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ አንድ ጠቅላላ የንግድ ድርጅት ወይም ሁለት ሀገሮች ሊመረጡ ይችላል ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ጋና በፈረንጆቹ 1960 ዎቹ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ማሰብ የጀመረች ቢሆንም ሂደቱ በመፈንቅለ መንግስት መበላሸቱ ተመላክቷል፡፡
ይሁንና በፈረንጆቹ 2006 የተከሰተውን ከባድ የኃይል ቀውስ ተከትሎ በዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ማህበር እርዳታ እቅዷን ዳግም ማነቃቃቷ ተገልጿል።
እንደ ሶግባጂ ገለጻ 16 ሀገራትና ኩባንያዎች የኒውክሌር ሃይል ማመንጫውን ለመገንባት በወጣው ጨረታ ቢወዳደሩም በኢነርጂ ሚኒስቴር የሚመራው የቴክኒክ ቡድን አምስት ሀገራትን ለይቷል።
በፈረንጆቹ 2034 ጋና ከኒውክሌር የሃይል አማራጭ 1 ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት ዕቅድ እንዳላት ጠቅሰዋል።