የደቡብ አፍሪካ ሀገራት ለኤልኒኖ ቀውስ 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የይገባናል ጥያቄ አነሱ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ አፍሪካ ሀገራት ለኤልኒኖ የአየር ንበረት ቀውስ 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የይገባናል ጥያቄ ማንሳታቸው ተሰምቷል፡፡
የደቡባዊ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ (ኤስኤዲሲ) የዝናብ እጥረትና ድርቅን የሚያስከትለው ኤልኒኖ እና መሰል የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክተው የሀገራት መሪዎች የበይነ መረብ ጉባኤ አካሂደዋል፡፡
በጉባኤውም ኤስኤዲሲ በኤልኒኖ ምክንያት በተከሰተው ድርቅ እና ጎርፍ ምክንያት ከ61 ሚሊየን በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጾ፤ በአባል ሀገራቱ የሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ነው የጠቆመው፡፡
ጉባኤውን ተከትሎ ኤስኤዲሲ በኤልኒኖ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው አባል ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሃብቶችን ለማሰባሰብ ቢያንስ 5 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቋል።
የኤስኤዲሲ እና አንጎላ ፕሬዚደንት የሆኑት ጆዎ ሎሬንኮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ የግሉ ዘርፍ፣ ግለሰቦች እና የኤስኤዲሲ አባል ሀገራት እንዲሁም ሌሎች በኤልኒኖ ለተጎዱትን ህዝቦች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ከፈረንጆቹ 2023 እስከ 2024 ዝናባማ ወቅት በአካባቢው የዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅ ኤስኤዲሲ በሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ እያለፈ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የወቅቱ የዝናብ መጠን ከደቡብና መካከለኛው አካባቢ በጣም ያነሰ እንደነበር ገልጸው፥ የቀጣናው ማዕከላዊና ደቡብ ምስራቅ ክፍሎች ለ50 ተከታታይ ቀናት እጅግ በጣም ደረቅ እና ሞቃት የዓየር ሁኔታዎች አጋጥሟቸዋል ነው የተባለው፡፡
ከአማካይ በታች ያለው የዝናብ መጠን የውሃ እጥረት አስከትሏል፣ ይህም በቂ ምርት እንዳይሰበሰብ አድርጓል፤ ለዱር እንስሳት አስፈላጊ የሆነውን የእፅዋት እድገት ቀንሷልም ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ንጽህና በጎደለው ውሃ የተነሳ የውሃ ወለድ በሽታዎችን መከሰቱን ገልጸው፥ ይህም በኤስኤዲሲ ቀጣና ውስጥ ባሉ በርካታ ሀገራት እየተስፋፋ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
አክለውም፥ አውሎ ነፋሶች እና ከአማካኝ በላይ የዝናብ መጠን እንደማዳጋስካር፣ ማላዊ እና ታንዛኒያ ባሉ አባል ሀገራት ላይ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ማስከተሉን ጠቁመዋል።
በጉባኤው ሥድስት የሀገር መሪዎችን ጨምሮ 15 ሀገራት የተሳተፉ ሲሆን፥ ዋና መሥሪያ ቤቱን በቦትስዋና ያደረገው ኤስኤዲሲ 16 አባል ሀገራትን ያቀፈ እንደሆነ የዘገበው ዢኑዋ ነው።