ጤና ሚኒስቴር 400 ሺህ ዶላር ዋጋ ያላቸው የሕክምና ማሽኖችን በድጋፍ አገኘ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሪች አናዘር ፋውንዴሽን በ400 ሺህ ዶላር የገዛቸውን አምስት የሕጻናት የጭንቅላት ሕክምና ማሽኖች (ኢንዶስኮፒ) ለጤና ሚኒስቴር አስረከበ፡፡
ማሽኖቹ በሕጻናት ጭንቅላት ውስጥ የሚጠራቀም ውኃ እና ሌሎች የሕጻናት የጭንቅላት ሕክምናን በኢንዶስኮፒ የማከም አግልግሎት እንደሚሰጡ ተገልጿል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሜዲካል አገልግሎት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኢሉባቡር ቡኖ እንዳሉት÷ ማሽኖቹ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ በሀገራችን የሕፃናት የጭንቅላት ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነቱ ይሻሻላል፡፡
ዛሬ የተረከብናቸውን ጨምሮ ከዚህ በፊት አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኙ ሶስት ኢንዶስኮፒ ማሽኖች ጋር በማድረግ አገልግሎቱን በስምንት ሆስፒታሎች ለማስፋት ይሠራል ብለዋል፡፡
ማሽኖቹ በሚቀጥለው ሣምንት ወደ ሐዋሳ፣ መቀሌ፣ ባሕር ዳር፣ ጅማ እና ሐረር ዩንቨርሲቲ ሆስፒታሎች እንደሚሰራጩ መገለፁን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡