Fana: At a Speed of Life!

ባህርዳር ከተማን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እየተሰራ ያለውን ስራ ማጠናከር ይገባል- አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባህርዳር ከተማን ለጎብኚዎችና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እየተካሄደ ያለው ልማት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የባህር ዳር ከተማ የተቀናጀ የመንገድ ዳር ልማትን በተመለከተ በተዘጋጀ ዲዛይን ዙሪያ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

ርዕሰ መስተድድሩ በዚህ ወቅት ÷ ባህር ዳር ከተማን ለነዋሪዎች፣ ለጎብኞችና ኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እየተካሄደ ያለውን ልማት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማን ተሞክሮ በመውሰድ ከከተማዋ የተፈጥሮ ፀጋ ጋር የተጣጣመ የመንገድ ዳር ልማት ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የዘርፉ ሙያተኞች የመንገድ ዳር ልማቱን ዘመኑን የዋጀ፣ የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ዲዛይን በማመቻቸት መተግበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ይህም በከተማዋ የሚተገበረው የተቀናጀ የመንገድ ዳር ልማት ለሌሎች ከተሞች ማስተማሪያና ተሞክሮ የሚወስድበት ተደርጎ መገንባት አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው ÷ በባህርዳር የሚካሄደው የመንገድ ዳር ልማት ከተማዋን ዘመናዊና ተመራጭ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ዲዛይን መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ መድረኩ የተሰናዳውም በዲዛይኑ ላይ በጥልቀት በመወያየትና ግብዓት በማሰባሰብ ፈጥኖ ወደ ስራ ለማስገባት ያለመ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.