በትግራይ ክልል ከ845 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ በጀት የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል መንግስት በመደበው ከ845 ሚሊየን ብር በላይ በጀት በትግራይ ክልል አምስት ከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን በጊዜያዊ አስተዳደሩ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለጸ።
የምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ በመቀሌ፣ በዓዲግራት፣ በዓድዋ፣ በአክሱምና በሽሬ እንዳስላሴ ከተሞች መጀመሩም ተገልጿል።
በቢሮው የምግብ ዋስትና ዳይሬክተር አቶ ተካ ተክለ እንደገለፁት÷ በፌዴራል መንግስት የተመደበው ከ845 ሚሊየን በላይ ብር የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በመርሃ ግብሩ የታቀፉ ከ84 ሺህ በላይ የከተሞቹን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።
ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግ በመርሃ ግብር ለታቀፉ ተጠቃሚዎች የክህሎት እና የፋይናንስ አያያዝ ስልጠና ባለፉት መጋቢትና ሚያዝያ ወራት ሲሰጥ ቆይቶ መጠናቀቁን አንስተዋል።
6 ሺህ የሚሆኑ አቅመ ደካማ ነዋሪዎችና ችግረኛ ህፃናት በቀጥታ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ዳይሬክተሩ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህም በስራ እድል ፈጠራና በከተሞች አረንጓዴ ልማት ላይ ከ16 ሺህ በላይ ዜጎች ስራ የጀመሩ ሲሆን÷ ቀሪዎቹ ከ68 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ደግሞ ወደ ስራ ሊያስገባቸው የሚችል ስልጠና ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
በምግብ ዋስትና መርሐ ግብሩ ከታቀፉት ነዋሪዎች ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም አቶ ተካ ገልፀዋል።