በቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደኅንነት ረቂቅ አዋጅ ላይ የግብዓት ማሰባሰብ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደኅንነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግብዓት ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ የሕግና የሳይበር ሙያተኞች ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የኢንፎርሜሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ሃኒማል ለማ በዚሁ ጊዜ÷ በቁልፍ የመንግሥት መሰረተ ልማቶችን የሳይበር ደኅንነት በማስጠበቅ ለዜጎች አገልግሎት ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ምኅዳር እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
የረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ተጠናቆ በሥራ ላይ ሲውል የመንግሥትን መሰረተ ልማትን ለመጠበቅ ግልጽ የሆኑ የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው መመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የሳይበር ሕግ ምርምርና ዝግጅት ዲቪዥን ኃላፊ ፍቅረሥላሴ ጌታቸው÷ረቂቅ አዋጁን በማጽደቅ ሥራ ላይ በማዋል ቁልፍ የመንግሥት መሰረተ ልማቶችን የሳይበር ደኅንነት የተጠበቀ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የሚገኘውን የዘርፉን ጥቃት መመከት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደኅንነት ረቂቅ አዋጅ ይዘት፣ ዓላማና ምንነት ለውይይት መነሻነት ቀርቦ ባለድርሻ አካላት ምክክር እያደረጉበት ይገኛል።