ቆሻሻን በዘመናዊ መልኩ ማስወገድና ለአፈር ማዳበሪያ ማዋል ውጤት እያመጣ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቆሻሻን በዘመናዊ መልኩ ማስወገድ እና ለአፈር ማዳበሪያ ማዋል አመርቂ ውጤት እያመጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ጅማ ከተማን ፅዱና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እንደ መንግስት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር)፤ ቆሻሻን ማስወገድ የማህበረሰቡን ጤንነት ማረጋገጥ ነዉ ብለዋል፡፡
ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በማልማት ሀብትን በተገቢው መጠቀም እንደሚቻል ገልጸው፤ በጅማ ከተማ ደረቅ ቆሻሻን በሳይንሳዊ መንገድ ለማስወገድና ለመጠቀም እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም ቆሻሻን እንደ ግብዓት በመጠቀም የአፈር ማዳበሪያ ኮምፖስት መስራት መጀመሩን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀይሉ ዳዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው ቆሻሻን በዘመናዊ መልኩ ማስወገድ እና ለአፈር ማዳበሪያ ማዋል አመርቂ ዉጤት እያመጣ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከተማን ዉብ፣ ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ጉልህ ሚና እንደሚወጣ በማንሳትም፤ ተሞክሮው ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋፋት ተስፋ የሚሰጥ ስራ ነዉ ብለዋል።
የጅማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አስራት እሸቱ (ኢ/ር) የከተማዋ ትልቅ ችግር የነበረዉን ደረቅ ቆሻሻ በዘመናዊ መልኩ መልሶ በማልማት ለተለያዩ ጥቅሞች እየዋለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህ ስራ ላይ ከ80 በላይ ማህበራትን በማደራጀት የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
በተስፋሁን ከበደ