ም/ጠ/ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮ-ቴሌኮም የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አገልግሎትን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢትዮ-ቴሌኮም ቦርድ ሰብሳቢ ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮ-ቴሌኮም የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አገልግሎትን ጎበኙ።
በጉብኝታቸውም የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ የደረሰበትን ደረጃ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘው የኢትዮ-ቴሌኮም የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ተገኝተው ተመልክተዋል፡፡
ኢትዮ-ቴሌኮም የነዋሪዎችን የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባን አዲስ አበባን ጨምሮ በ29 ከተሞች በሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላቱ በቅርቡ ማስጀመሩ ይታወቃል፡፡
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ 2018 ዓ.ም መጨረሻ ለ90 ሚሊየን ዜጎች ዲጂታል መታወቂያን ለማዳረስ መታቀዱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከዚህም ውስጥ ኢትዮ-ቴሌኮም በወር በአማካይ 1 ሚሊየን ዜጎችን በመመዝገብ ለ32 ሚሊየን ዜጎች ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ዕቅዱን 36 በመቶ እንደሚያከናውን ገልጿል።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ ከሚያስፈልጉ አስቻይ ሥርዓቶች ውስጥ አንዱ መሆኑና ለአካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተመላክቷል፡፡