Fana: At a Speed of Life!

የባህላዊ ፍርድ ቤት የዜጎችን መብት በማስከበር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የባህላዊ ፍርድ ቤት የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና የዜጎችን መብት በማስከበር ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

እንዲሁም በተለያዩ አካላት መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በባህላዊ ሕጎች ከመፍታት በተጨማሪ እውነት በማውጣትና ፍትህ በማስፈን፣ የተፋላሚ ወገኖችን ማህበራዊ መስተጋብር መልሶ በማንሰራራት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የክልሉ ህብረተሰብ ተደራሽ፣ በቀላል ሂደትና ወጪ ቆጣቢ መንገድ የሚገኝ የፍትህ አገልግሎት እንዲቀርብለት፣ የህግና የፍትህ ስርዓቱ ሂደት ለኦሮሞ ባህልና ወግ መጎልበት እንዲረዳ፣ እንዲሁም የባለቤትነት ስሜት እንዲያብብ በማስቻል ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ካሉ 7,477 ቀበሌዎች፣ 6,355 ቀበሌዎች እስካሁን በተመሰረቱ 6,252 የመጀመሪያ ደረጃ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ስር ተደልድለው አገልግሎት እያገኙ ነው። በሌላ በኩል በ333 ወረዳዎች፣ 355 ይግባኝ ሰሚ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች መቋቋማቸውንም ገልፀዋል፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ባህል ፍርድ ቤቶችን የመዝገብ ሂደት ስንመለከት፣ ባለፉት 9 ወራት 352,168 መዝገቦች ቀርበው 287,165 የሚሆኑት (81.54%) ውሳኔ አግኝተዋል ብለዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ እንዳሉት የ2015 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት የመዝገብ ፍሰት 260,382 የነበረ ሲሆን÷ ከ2016 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ጋር ሲነጻጸር፣ በመካከላቸው የ91,786 (35.25%) ልዩነት ይገኛል።

በሌላ በኩል፣ ይግባኝ ሰሚ ባህል ፍርድ ቤቶች 17,984 መዝገቦችን ተቀብለው 15,038 (83.62%) ለሚሆኑ መዝገቦች ውሳኔ ሰጥተዋል፤ የ2015 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት፣ 12,051 መዝገቦች ሲሆኑ፣ ከ2016 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ጋር ሲነጻጸር በመካከላቸው የ5,933 (49.23%) መዝገቦች ልዩነት ይታያል ነው ያሉት።

የመጀመሪያ ደረጃ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ስንመለከት፣ የ2015 ዓ.ም 209,270 (80.37%) መዝገቦች ውሳኔ የተሰጣቸው ሲሆን በዘንድሮ ዓመት ደግሞ 287,165 (81.54%) መዝገቦች ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል።

ይግባኝ ሰሚ ባህላዊ ፍርድ ቤት የ2015 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም 8,800 (73.02%) መዝገቦች ሲሆን የዘንድሮ ተመሳሳይ ወቅት ደግሞ 15,038 (82.52%) ደርሷል ብለዋል።

በዚሁ መሠረት የሁለቱም ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ደረጃዎች በ2016 ዓ.ም ዘጠኝ ወራት ውሳኔ ያገኙ መዝገቦች ቁጥር ከ2015 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው የ6,238 (70.88%) ብልጫ ማሳየቱን አቶ ሽመልስ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡

“በአጠቃላይ ሂደቱ የባህል ፍርድ ቤቶች በአንድ ወገን መዝገቦችን ከእጃቸው የማጣራት አቅም እያጎለበቱ መምጣታቸውን፣ በሌላ ወገን መፍትሄ እየሰጧቸው የሚገኙ የግላዊና ማህበራዊ ችግሮች ቁጥር እጅግ ብዙ መሆኑን የሚያረጋግጥልን ነው” ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ባህላዊ ፍርድ ቤቶች መንግስት የጀመረውን የበለጠ እንዲደራጁና ተቋማዊ መልክ እንዲይዙ የማገዝ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.