የብሪክስ ጥምረት የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ለማስፋትና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማሳደግ ይረዳል – አምባሳደር ዲና
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የብሪክስ ጥምረት ኢትዮጵያ በዓለም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዕድሎችን እንድታሰፋና ኢኮኖሚያዊ ትብብሯን እንድታጠናከር ያደርጋል ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የደቡብ ደቡብ ትብብርን በማስተዋወቅ ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነት የሚኖራትን ሚና፣ ዕድልና ቀጣይ ስራ የሚዳስስ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
አምባሳደር ዲና እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነት በንግድ፣ ቱሪዝም፣ የገንዘብ ድጋፍ፣ ቴክኖሎጂና መሰል መስኮች በሚኖራት ተጠቃሚነት ላይ ምክክር ተደርጓል።
የኢትዮጵያን የብሪክስ ጥምረት ተጠቃሚነት ለማስጠበቅም የውስጥና የውጭ ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችል የአሰራር መርሆችን መከተል ያሰፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በብሪክስ የትብብር ጥምረት ጠንካራ አባል ሆና ለመዝለቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልጋት ምክረ ሃሳብ መቅረቡንም ተናግረዋል።
የብሪክስ ጥምረት የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ የግንኙነት ዕድሎችን በማስፋት በትብብር የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማሳለጥ እንደሚያስችልም አመላክተዋል።
ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም ባለቤት የሆኑት ሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድና ብራዚል በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ብዝሃ የኢኮኖሚ መስኮች መነቃቃት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ነባርና በአዲስ መልክ ጥምረቱን የተቀላቀሉ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር በመርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ስላላቸው ኢትዮጵያ የብሪክስ አዲስ የልማት ባንክን ጨምሮ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስገኝላት መጠቆማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ኢትዮጵያ ጥምረቱን መቀላቀሏ የኢትዮ-ሩሲያን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በማጠናከር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ ጠቁመዋል።