Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ በግብጽ ሚዲያዎች የሚነዛው የሀሰት መረጃ የዓባይን ውሃ ለብቻ የመጠቀም ራስ ወዳድነት ነው – መሀመድ አልአሩሲ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በግብጽ ሚዲያዎች የሚነዛው የሀሰት መረጃ የዓባይን ውሃ ለብቻ የመጠቀም ራስ ወዳድነት ነው ሲሉ በግድቡ ዙሪያ በዓለም አቀፍ መድረኮች በመሟገት የሚታወቁት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ መሀመድ አልአሩሲ ገለጹ።

ከሰሞኑ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል በሚል መነሻነት የግብጽ ሚዲያዎች ግድቡ አደጋ ያጋጥመዋል በሚል ሀሰተኛ መረጃ በመንዛት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ግድቡ በተፋሰሱ ሀገራት ላይ አንድም ጉዳት እንደማያደርስ ሁሉም የሚያውቀው ሀቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት መሀመድ አልአሩሲ፤ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ሕጋዊ እና ቴክኒካዊ ቡድን እንዲሁም የውሃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የየሀገራቱ ከፍተኛ መሪዎች ጭምር የተሳተፉባቸው ውይይቶች መካሄዳቸውን አስታውሰዋል።

የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል በሚል አሁን በግብጽ ሚዲያዎች የሚነዛው የሀሰት መረጃ መነሻው የቀድሞው የቅኝ ግዛት ውል ተፈጻሚነት ፍላጎት እና የዓባይን ውሃን ለብቻ የመጠቀም ራስ ወዳድነት ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሁሉም መድረኮች በጋራ የመጠቀም አቋምን መያዟን አስታውሰው፤ ግብፅ መከራከሪያ አድርጋ የምታቀርበው የዓባይን ወንዝ በበላይነት የመቆጣጠር “የቅኝ ግዛት ውል” ኢትዮጵያ የማታውቀው፣ የማትቀበለው፣ ለአንዱ ወገን ያደላ፣ ጊዜውንም የማይመጥን ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

የግብጽ መንግስት የዜጎቹን ልብ ለመግዛት የሚጠቀምበት ፕሮፓጋንዳ በፍጹም ለዚህ ዘመን የማይመጥን እና ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

ግድብ በግብፅም ሆነ በሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ጉዳት እንደማያደርስ በተደጋጋሚ ውይይት ተደርጎ ከስምምነት የተደረሰበት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህ እየታወቀ የግብጽ ሚዲያዎች በየወቅቱ የሚያሰራጩት የሀሰት መረጃ በኢትዮጵያ የወደፊት የመልማት ጉዞ ላይ ጫና ለማሳደር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ድርጊት ከንቱ ፍላጎት ካሆነ በስተቀር፣ የሚሆን ጉዳይ አይደለም ያሉት መሐመድ አልአሩሲ፤ ኢትዮጵያ አቋሟ አሁንም ወደፊትም “በጋራ እንጠቀም” የሚል መርህ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ግድቡ በተፈጥሮ ሀብት የመልማት መብት ነጸብራቅ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ሀብት መፍጠር፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ብልጽግና ማረጋገጥ የሚችል ወሳኝ ሀገራዊ ሀብታችን ነውም ብለዋል፡፡

የግድቡን ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን እንደ ዳግማዊ ዓድዋ በማየት ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጊዜያቸውን ሳይሰስቱ ያፈሰሱበት ነው ብለዋል አቶ መሀመድ አላሩሲ፡፡

ግድቡ እስኪጠናቀቅም ይኸው ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልፀው፤ ግድቡ ከራስ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ከፍተኛ የልማት አቅም እና አማራጭ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡

ስለሆነም ግብጽ የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ዜጎቿን ግራ በማጋባት ከምትጠመድ በጋራ ለመልማት እና ለመጠቀም ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ብትሰራ መልካም መሆኑን አመላክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.