የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጦር መሣሪዎችን ምልክት በማድረግ ወደ መረጃ ቋት ማስገባት ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የጦር መሣሪያዎችን ምልክት በማድረግ ወደ መረጃ ቋት ማስገባት ጀመረ፡፡
ፌደራል ፖሊስ የጦር መሣሪያን ምልክት በማድረግ ወደ ጦር መሣሪያ መረጃ ቋት ማስገባት ላይ ያተኮረ ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጦር መሣሪያ ፍቃድ እና ጥበቃ ተቋማት ቁጥጥር መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ዘካሪያስ ይርጋለም በወቅቱ እንደገለጹት÷ የጦር መሣሪያ ቁጥጥርና ክትትልን የተሳለጠ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አመራርና አባላት እጅ የሚገኝ፣ በግምጃ ቤት የተቀመጠ፣ ለፌደራል ፖሊስ ለግለሰብና ለተቋማት የተሰጡ መሣሪያዎች፣ በሕገ-ወጥ ዝውውር የተያዙ እና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተወረሱ እንዲሁም አገልገሎት የማይሰጡ መወገድ ያለባቸው የጦር መሣሪያዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሕግና ሰብአዊ መብቶች መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ፋሲል አሻግሬ÷ የግለሰብን፤ የቤተሰብን እንዲሁም የሀገርን ደህንነት እና ሉአላዊነት ለመጠበቅ እና ከጥቃት ለመከላከል ሕግን መሰረት ያደረገ የጦር መሣሪያ አጠቃቀም ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ስልጠናዉ ሲጠናቀቅም የጦር መሣሪያ ዳታን በአንድ የመረጃ ቋት በመያዝ በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመለየት ይሰራል መባሉን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።