በአማራ ክልል ሰላም እየሰፈነ በመምጣቱ የልማት ሥራዎችን በስፋት ማከናወን መቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰላም እየሰፈነ በመምጣቱ የልማት ሥራዎችን በስፋት ማከናወንና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን አጠናቅቆ ማስመረቅ መቻሉን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ሃላፊ መንገሻ ፈንታው(ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ÷ባለፈው ሳምንት በጎንደር ከተማ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ አመራሮች መድረክ፣ በጎርጎራ የተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባና የባህር ዳር ከተማ የአዲሱ የዓባይ ድልድይ ምረቃ ሥነ ስርዓት መካሄዱን አስታውስዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት በሰሜን ሸዋ ዞን በቡልጋ ከተማ አስተዳደር የተገነቡ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማስመረቅ መቻሉን አስረድተዋል።
በክልልና የዞን አመራር አባላት መሪነትም በየአካባቢው በሚገኙ ከተሞች በርካታ የልማት ሥራዎች ግንባታ ጉብኝትና የማስመረቅ ስራ የተከናወነበት ሳምንት መሆኑን ገልጸዋል።
ከተከናወኑ ሁነቶች ውስጥም ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተገነባው ዘመናዊው አዲሱ የዓባይ ድልድይ ለክልሉም ሆነ ለሀገር የሚኖረው ማህበራዊና ኢኮኖሚ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ድልድዩ የንግድና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን በማጠናከር የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ መሰረት እንደሆነ መጥቀሳቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በድልድዩ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ በአንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያዎች ችግር ተፈጥሯል ተብሎ የተናፈሰው ወሬ ፍጹም ሃሰት ነው ያሉት ሃላፊው ÷ ሥነ-ሥርዓቱ በርካታ ህዝብ የተሳተፈበትና ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ የተጠናቀቀ መሆኑን አብራርተዋል።
በሃሰት ፕሮፖጋንዳ የህዝብን ልብ መግዛትም ሆነ ድል እንደማይገኝ ገልፀው ÷ከዚህ ይልቅ ለሀገርና ለህዝብ የሚበጀውን የሰላም አማራጭ መከተል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።