Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል ገለጹ።

ሚኒስትሯ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም አስመልክተው ባቀረቡት ሪፖርት፤ ሚኒስቴሩ የመጀመሪያውን የተቋም ግንባታ ምዕራፍ አጠናቆ ወደ ሁለተኛ ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልፀዋል።

የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን በማካተት “ዓመተ-ምርታማነት” የሚል ስያሜ በመስጠት እያንዳንዱ ሥራዎች ወደ ውጤት መቀየር አለበት የሚል እሳቤ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልፀው፤ በክህሎት ልማት ዘርፍ ፍላጎት መር ሥርዓተ-ሥልጠና መስጠት ላይ ትልቅ ሥራ መከናወኑን አመላክተዋል።

በቴክኒክና ሙያ ተቋማት አዳዲስ ካሪኩለም የመቅረጽ እና ጊዜውን የዋጀ የካሪኩለም ክለሳ መደረጉን አንስተው፤ በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች ፍላጎት መር ሥልጠና መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

የሥራ ፈጠራ በልቶ የማደር ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን እና ይልቁንም ሀብት መፍጠሪያ መንገድ መሆኑን አንስተዋል።

የስራ ዕድል ፈጠራው ከግብርና ልማት፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከኢንቨስትመት እንዲሁም ከአገልግሎት ዘርፍ ጋር ማስተሳሰር መቻሉንም አስረድተዋል።

የግብርናው ዘርፍ ስራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፤ የኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ዘርፍ የተሻለ የስራ ዕድል የተፈጠረባቸው እንደሆነ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ክህሎት መር እሳቤ በመተግበር ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የገበያ መረጃ ሥርዓት ለአፈጻጸሙ ጉልህ አስተዋጽዖ ማበርከቱንም ተናግረዋል።

መንግስት ለስታርትአፕ በሰጠው ልዩ ትኩረት በዘርፉ ከፍተኛ የስራ ዕድል መፍጠር እንዳስቻለ ገልጸው፤ ስታርትአፕ በርካታ የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል በመሆኑ በቀጣይ በልዩ ትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም አመላክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.