በመድኃኒት ቤቶችና መደብሮች ላይ አስገዳጅ ደረጃ ሊተገበር ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ መድኃኒት ቤቶችና መድኃኒት መደብሮች ላይ አስገዳጅ ደረጃ በቅርቡ ሊተገበር መሆኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ አስታወቁ፡፡
በመድኃኒት ቤቶችና መድኃኒት መደብሮች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ሀገር አቀፍ አስገዳጅ ደረጃ መውጣቱን ጠቅሰው÷ አስገዳጅ ደረጃው መድኃኒት ቤትም ሆነ መድኃኒት መደብር ስለሚኖራቸው ባለሙያዎች፣ ስለሚይዙት የመድኃኒት ዓይነት፣ ስለ መድኃኒት ቤቱ ወይም መደብሩ ስፋትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ማካተቱን አብራርተዋል፡፡
ክልሎች ለመድኃኒት ቤትና መድኃኒት መደብር ፈቃድ የሚሰጡበት መስፈርት የተለያየ መሆኑን አስገንዝበው ÷ አሠራሩን ወጥነት ያለው ለማድረግ ደረጃው መዘጋጀቱን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
የአስገዳጅ ደረጃውን መውጣት ተከትሎም አሠራሩ እስከሚተገበር ድረስ ለአዲስ መድኃኒት ቤትና መድኃኒት መደብር ፈቃድ እንዳይሰጥ መደረጉንም አረጋግጠዋል፡፡