የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባው አዲሱን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቋል፡፡
የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ የውሳኔ ሃሳቡን ለምክር ቤቱ በንባብ ያቀረቡ ሲሆን ፥ የረቂቅ አዋጁን መሻሻል አስፈላጊነት እና በምርመራው ሂደት የተከናወኑ ተግባራትንም በዝርዝር ለጉባኤው አስረድተዋል፡፡
አዋጁ የአርሶና አርብቶ አደሩን እና ከፊል አርብቶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ሀገሪቱ ከደረሰችበት ዘርፈ ብዙ እድገት ጋር እኩል ለማራመድ የሚያስችል መሆኑ መገለጹን ከምክርቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የተፈጥሮ ሃብቶችን በዘላቂነት በመጠበቅና በማልማት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ፣ የሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት ማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ረቂቅ አዋጁ በምክርቤት አባላት ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1324/2016 አድርጎ አፅድቆታል፡፡