በኢንዶኔዥያ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ የ41 ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንዶኔዥያ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የ41 ሰዎች ህይወት ማለፉን የሀገሪቱ አደጋ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
አደጋው በሀገሪቱ ለሰዓታት የዘለቀውን ዝናብ ተከትሎ የተከሰተ ሲሆን፤ በሱማትራ ደሴት ውስጥ በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ተብሏል፡፡
የጎርፍ አደጋው ቤቶችን ማጥለቅለቁ የተገለፀ ሲሆን በአደጋው እስካሁን 41 ሰዎች ሲሞቱ 17 ሰዎች ደግሞ የት እንዳሉ ማወቅ አለመቻሉ ነው የተገለፀው፡፡
በተጨማሪም በአደጋው በሰው ህይወትና በቤቶች ላይ ካደረሰው ጉዳት በተጨማሪ 16 ድልድዮችና 20 ሄክታር የሩዝ ማሳ ላይ ውድመት ማስከተሉ ተነግሯል።
የነፍስ አድን ሰራተኞች የጠፉ ሰዎችን እያፈላለጉ እና የአደጋው ተጠቂዎችን ከአካባቢው የማስወጣት ስራ እያከናወኑ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
እስካሁን በተደረገ ጥረት 130 ሰዎችን ከአደጋው በማትረፍ በትምህርት ቤት እንዲጠለሉ ማድረግ የተቻለ ሲሆን 2 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን ደግሞ በጊዜያዊ መጠለያዎች እና በተለያዩ ቦታዎች እንዲያርፉ መደረጉን ቲ አር ቲ ዘግቧል፡፡