የዓሳማ ኩላሊት የተለገሰላቸው ግለሰብ ህይዎታቸው አለፈ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጀመሪያ ጊዜ የዓሳማ ኩላሊት ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው ግለሰብ ከሆስፒታል አገግመው ከወጡ ከሁለት ወራት በኋላ ህይዎታቸው ማለፉ ተሰምቷል፡፡
የ62 ዓመቱ ሪቻርድ ስሌይማን የኩላሊት ህመም እንዳለባቸውና በአፋጣኝ የኩላሊት ንቅለተከላ ማድረግ እንዳለባቸው ተነግሯቸው ዲያሊሲስ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
በዚህም ለግለሰቡ በአሜሪካ ማሳቹሴትስ አጠቃላይ ሆስፒታል ለመጀመሪያ ጊዜ የዓሳማን ኩላሊት ለሰው ልጅ በንቅለ ተካላ የተደረገላቸው ከሁለት ወራት በፊት እንደነበር ዘግበን ነበር፡፡
ከአሁን በፊት ተሞክሮ ያልተሳካው የዓሳማ ኩላሊት ንቅለ-ተከላ ጊዜው ደርሶ በዘርፉ ሊቆች ታግዞ የግለሰቡን ህይዎት ያተርፋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበትም ነበር፡፡
የንቅለ-ተከላ ሂደቱ አራት ሰዓታት እንደፈጀ የተናገሩት ሃኪሞች ፥ በወቅቱ የዓሳማው ኩላሊት ከግለሰቡ ተዋህዶ በአግባቡ እየሰራ መሆኑን በማረጋገጥ ከሆስፒታል እንዲወጣ መደረጉ ይታወሳል፡፡
ስሌይማን በበኩላቸው ፥ “ህክምናው ተሳክቶ ወደቤቴ መመለሴ የሕይወቴ ትልቁ ደስታ ነው” በማለት ስሜታቸውን ገልፀው ነበር፡፡
ሆኖም ለህክምናው ዘርፍ ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት አስተዋጽዖ ያደረጉት ይህ ግለሰብ ከተሳካ ቀዶ ህክምናው ከሁለት ወራት በላይ መቆየት አልቻሉም፡፡
ሱሌይማን ከኩላሊት ህመም በተጨማሪ ዓይነት 2 የስኳር በሽታ እና የደም ግፊት የነበረባቸው ሲሆን ፥ የሞታቸው ምክንያት የኩላሊት ንቅለ ተከላው ነው የሚል ፍንጭ እንደሌለም ነው የተነገረው፡፡
ግለሰቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ህሙማን የተስፋ ብርሃን ሆኗል ያለው ሆስፒታሉ ፥ ‘ዜኖትራንስፕላንቴሽን’ ወይንም የሌሎች እንስሳትን የውስጥ አካል ክፍሎች ለሰው ልጅ የማድረግን ህክምና ወደፊት ለማራመድ ላሳዩት እምነትና ፈቃደኝነት አመስግኗል፡፡
በዚህም ስሌይማን ለዘርፉ የህይዎት መስዕዋዕትነት በመክፈል ላሳዩት ድጋፍ ስማቸው ሲነሳ ይኖራል ፤ ግባቸውንም አሳክተዋል መባላቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡