አቡነ ሉቃስ በተከሰሱበት የቅስቀሳ ወንጀል ጥፋተኛ ተባሉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አቡነ ሉቃስ በተከሰሱበት የቅስቀሳ ወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው።
ተከሳሹ ጥፋተኛ የተባሉባቸው ሁለት ክሶች በአንቀጽ 247 (ሐ) ስር ተጠቃሎ ነው።
የጥፋተኝነት ፍርዱን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ህገመንግስታዊና በህገመንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች የሚመለከተው ችሎት ነው።
የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በአቡነ ሉቃስ ላይ ከ3 ወራት በፊት ሁለት ክሶችን ማቅረቡ ይታወሳል።
ይህም ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 247 (ሐ) እና አንቀጽ 258 (ሀ) ስር እና የወንጀል ህግ አንቀጽ 251 (ሐ) የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚሉ ሁለት ክሶች ነበሩ።
በቀረበባቸው ክስ ላይ፤ ተከሳሹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የምስራቅ አዉስትራሊያ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ በጠቅላይ ቤተክህነት የገዳማት መምሪያ የበላይ ሃላፊ ሊቀጳጳስ ሆነዉ በጵጵስና በማገልገል ላይ እያሉ ስለ ሰላም እና አንድነት የመስበክ ሃይማኖታዊ ግዴታቸዉን ወደ ጎን በመተዉ በታህሳስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገረ አሜሪካ ቴክሳስ እና አካባቢዉ በሚገኝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቤተክርስቲያን ታቦት ወጥቶ በቆመበት አዉደምህረት ላይ በመገኘት የአመፅ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ዐቃቤ ሕግ በዝርዝር ጠቅሷል።
በዚህ በቀረበባቸው ክስ ላይ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በሌሉበት የተከሰሱባቸው ክሶች በአንቀጽ 247 (ሐ) ስር ተጠቃሎ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ የቅጣት አስተያየት ለመጠባበቅ ለግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ