Fana: At a Speed of Life!

ቀዳሚ አጀንዳችን ሕግን በማስከበር የልማት እንቅስቃሴን ማስቀጠል ነው – አቶ እንዳሻው ጣሰው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሉ ቀዳሚ አጀንዳ ሕግን በማስከበር የልማት እንቅስቃሴዎችን ቀጣይነት ማረጋገጥ ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የሰላምና ጸጥታ ሥራዎች የግምገማ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።

አቶ እንዳሻው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት÷ የሰላምና ጸጥታ ስጋቶች ተወግደው ሕዝቡ ሙሉ ትኩረቱን ወደ ሁለንተናዊ ልማት ማዞር አለበት።

ለዚህ ደግሞ የጸጥታ መዋቅሩ መጀመሪያ ማስተማር ከዚህ ባለፈም ሕግን ማስከበር ላይ ገለልተኛ ሆኖ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የጸጥታ ሁኔታው መሻሻል እያሳየ መሆኑን በመግለጽ የሰላም ሁኔታውን መሰረት ማስያዝና ማጽናት እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብ ይገባል ያሉት አቶ እንዳሻው÷ ሕዝቡ በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በልማትም መቀናጀት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ንግድንና ሕገ-ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር የተደረጉ ጥረቶች ውጤታማ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በቀሪው ሩብ ዓመትም በየደረጃው ያሉ የጸጥታ ምክር ቤቶችን ማጠናከር፣ የሰላም ጠንቅ የሆኑ ጉዳዮችን በጥናት ለይቶ የመፍትሔ ርምጃዎችን መውሰድ፣ ሰላምን የማጽናት፣ ግጭት ቀስቃሽ በሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግሮች ላይ ሕጋዊ ርምጃ የመውሰድ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል፡፡

ለዚህ ስኬትም የመረጃ ሥርዓትን የማጠናከርና ማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ሥራ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ነው ያመላከቱት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.